በአብዱልመናን መሐመድ
የኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ በተለያዩ ወቅቶች የተለያዩ ባንኮችን ምስረታ አስተናግዷል። እነዚህ ሁነቶች በአብዛኛው ከፋይናንስ ፖሊሲ ለውጦች ጋር የተያያዙ ናቸው። በ1990ዎቹ (እ.አ.አ) መጀመሪያ የተደረገው ማሻሻያ የፋይናንስ ዘርፉን ለግል ኢንቨስትመንት በመፍቀዱ በባንክ ኢንዱሰትሪው ውስጥ የግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ መሰረት ጥሏል። ከዚያ ቀጥሎ በነበሩ ተከታታይ አመታት ብዙ ባንኮች ተመስርተዋል። ከረጅም ጊዜ አልፎ አሁን ባለው ሁኔታ ደግሞ ባለፋት ጥቂት አመታት ብቻ በባንክ ዘርፉ አትራፊነት በመሳብና በአበረታች የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን በመነሳሳት ብዙ አዳዲስ ባንኮች ተመስርተዋል። አሁን ላይ 20 ባንኮች በስራ ላይ የሚገኙ ሲሆን ፣ ከእነዚህ ሁለቱ የመንግስት የተቀሩት ደግሞ የግል ባንኮች ናቸው።
የግል ባንኮች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረ ቢሆንም፣ በኢንዱስትሪው ውስጥ ጉልህ ድርሻ ያለው ግን በመንግስት ባለቤትነት የተያዘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነው። ባንኩ ከአጠቃላይ የገበያ ድርሻ (በሀብት) 60 በመቶ ይይዛል። ከተመሰረቱ ረጅም አመት ያስቆጠሩ አንጋፋ የግል ባንኮችም በኢንዱሰትሪው የራሳቸው ሰፊ ድርሻ አላቸው። ታዲያ በዚህ የገበያ ስርአት ውስጥ ያሉ አዳዲስ የግል ባንኮች ቀሪውን አነስተኛ የገበያ ድርሻ ለመቀራመት እንዲፎካከሩ ይገደዳሉ። ይህም የገበያ ውድድር፣ የፋይንናስ መረጋጋትና አካታችነት ላይ ተጽእኖ ይኖረዋል።
የባንኮች ቁጥር መጨመር ውድድርን እንደሚፈጥር ይታመናል። ይህ ውድድር ደግሞ የፋይናንስ አገልግሎቶች ተደራሽነት ያሰፋል ፣ የወለድ ህዳግ (በብድር እና ቁጠባ መካከል ያለው የወለድ ምጣኔ ልዩነት) እንዲጠብ ያደርጋል፣ የደንበኞች ግልጋሎትን ያሻሽላል እንዲሁም አዳዲስ የአሰራር ፈጠራዎችን ያበረታታል።
ነገር ግን እነዚህ ውድድር ያመጣቸዋል ተብለው የሚታሰቡ ትሩፋቶች በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ አወቃቀር ምክንያት እውን ያለመሆን እድላቸው በግልጽ ይታያል።
የኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ግልጽ የሆኑ የገበያ ክፍፍሎች የሚታይበት ነው። የኢትዮጵያ ንግድ ባንከ እምብምዛ አማራጭ ለሌላቸው የመንግሥት አካላትና ፕሮጀክቶች ብድር ይሰጣል እንዲሁም ከዚሁ ዘርፍ አነስተኛ የወለድ የሚከፈልባውቸን ተቀማጭ ሂሳቦችን ይሰበስባል። የግል ባንኮች ደግሞ የግል ዘርፉን ያገለግላሉ። በዚህ የኢንዱስትሪው የተነጣጠለ ባህሪ የተነሳ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በብቸኝነት የባንኮችን የዋጋ አወሳሰን የሚዘውር ይመስላል (monopolistic pricing conduct)። ይህ የንግድ ባንኩ ባህሪ ከኢንዱስትሪው ፍፁም ተመሳሳይ የሚመስል የባንክ አገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተዳምሮ የሌሎች ባንኮች የዋጋ አሰራር ላይ ደንበኞቻቸውንም ተጠቃሚ በማያደርግ መልኩ ተፅእኖ ያሳድራል። ከነዚህ ውስጥም አነስተኛ ወለድ፣ የብድርና ቁጠባ ምጣኔው ልዩነት መስፋትን ማንሳት ይቻላል።
ሆኖም፣ ሁሉም ባንኮች የተለያየ የዋጋ አተማመን ያላቸው ቢሆንም፣ የተቀማጭ ቁጠባ ለመሰብሰብ እና የውጭ ምንዛሬን ለማግኘት ከፍ ያለ ፉክክር እንዳለ ይታያል። ከተለያዩ የማስታወቂያ ስራዎቻቸው በተጨማሪ እነኚህ ባንኮች ቅርንጫፎቻቸውን በማስፋት ተቀማጭ የሚያደርጉ ደንበኞችን ለመድረስ ይሞክራሉ። ይህ የባንኮች ተለምዷዊ አሰራር ወጪው ከፍተኛ ነው። አዳዲሶቹ ባንኮችም ይህንኑ አሰራር ይዘው የሚመጡ ከሆነ ውድድሩ እጅግ የበረታ ይሆናል። ይልቁንም ይህ ውድድር በዋነኝነት ዝቅተኛ አቅም ያላቸው ባንኮች ላይ ተፅእኖ ያሳድራል። እንዲህ ያለው ውድድር የፋይንናንስ አለመረጋጋትን ሊፈጥር ስለሚችል የኢንዱስትሪውን ተቆጣጣሪዎች ሊያሳስብ የሚገባ ጉዳይ ነው።
የባንኮች ቁጥር መጨመር የፋይናንስ አካታችነትን እንደሚያሳድገው ምንም ጥርጥር የለውም። ኢትዮጵያ አካታች የፋይናንስ ዘዴዎች እና ስርአት በመፍጠር ረገድ እንደ ኬንያ ካሉ ጎረቤቶቿና ሌሎች ብዙ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሃገራት አንጻር ወደኋላ ቀርታለች። የባንክ ዘርፉ መደበኛ (conventional) አገልግሎቶች ዋነኛ ድክመት በኢ-መደበኛ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው የሚገኙ እንዲሁም በሃገሪቱ የገጠር አካባቢዎች የሚኖሩ ማህበረሰቦችን (ምንም እንኳን ከሃገሪቱ ህዝብ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙ ቢሆንም) ተደራሽ አለማድረጋቸው ነው።
የፋይናንስ አካታችነት እንዲሻሻል ከተፈለገ የፋይናንስ ተቋማት የሚሰጧቸው አገልግሎቶች በዲጂታል ፋይናንስ አማራጮች የታገዙ ሊሆን ይገባል። ለምሳሌ፣ በኬንያ በ2007 (እ.አ.አ) የተጀመረው የኤም-ፔሳ የኬንያ ዲጂታል ፋይናንስ አብዮት ምልክት መሆን ብቻ ሳይሆን የሃገሪቱን የዲጂታል ፋይናንስ ስርአት በሰፊው የለወጠ ሆኗል። በተንቀሳቃሽ ስልክ የሚተገበር የገንዘብ ክፍያ አማራጭ ሆኖ የጀመረው ኤም-ፔሳ ፣ በመደበኛው የፋይናንስ ስርአት ተጠቃሚ መሆን ላልቻሉ ሰዎች ዘርፈብዙ የፋይናንስ አገልግሎቶችን ወደመስጠት አድጓል። ይህ የዲጂታል ፋይናንስ እድገት የሃገሪቱ ዜጎች በቀላሉ የገንዘብ ክፍያ እንዲያደርጉ ፣ ገንዘብ እንዲያስተላልፉና ተቀማጭ እንዲያደርጉ ብሎም የኢንቨስትመንትና ኢንሹራንስ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ አስችሏል።
ባለፈው አስር አመት ውስጥ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ስርአት ወደ ዲጂታል የመሻገር ጉዞውን ጀምሯል። መነሾ የሆነው “በኢትዮጵያ የብሔራዊ ክፍያን የማዘመን ስትራቴጂካዊ ማእቀፍ” በግንቦት ወር 2009 (እ.አ.አ) መውጣቱ ነው። ከዚህ በመቀጠል “የብሔራዊ የክፍያ ስርዓትን” ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ደግሞ “የብሔራዊ የክፍያ ሥርዓቱን ደህንነት፣ አስተማማኝነትና ቅልጥፍና ለማረጋገጥ” የሚረዱ የመቋቋሚያ፣ የአሰራርና አስተዳደር ድንጋጌዎችን የያዘ ነው። ይህ አዋጅ ቀጥሎ ከወጡ መመሪያዎችና ማሰፈጸሚያዎች ጋር በመሆን ለዲጂታል ጉዞው መሰረት ጥሏል።
ባለፋት አስር አመታት የፋይናንስ ስርአቱ እንዲሻሻል መደላድሎች ተፈጥረዋል። የክፍያ ስርአቱን ዘመናዊ ለማድረግ ከ2010 ወዲህ ባሉ የመጀመሪያ አመታት ጅምሮች ታይተዋል። በ2011 (እ.አ.አ) የብሔራዊ ባንክ የኢትዮጵያ ባንኮች በማስተሳሰር ከአንዱ ባንክ ወደ ሌላኛው የገንዘብ ክፍያና ልውውጦች እንዲኖር የሚያስችለውን አሰራር (EATS)” አስጀምሯል። ከዚያ በመቀጠልም ባንኮች በኮር ባንኪንግ ስርአት የገንዘብ ዝውውር እና ካርድ ክፍያን በኤ.ቲ.ኤምና ፖስ ማሽኖች መፈፀም እንዲሁም የኢንተርኔትና ሞባይል ባንኪንግ አገልግሎቶች መስጠት ጀምረዋል። በቅርቡ ደግሞ የሞባይል የገንዘብ አማራጮችን ለማሳደግ በመንግሥት ይዞታ ስር የሆነው ቴሌ-ብር የተሰኘው አገልግሎት በ2021 (እ.አ.አ) አጋማሽ የተጀመረ ሲሆን አንድ የግል የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ሰጪም በተመሳሳይ ፍቃድ አግኝቷል።
ነገር ግን ፣ ምንም እንኳን የህግና ቁጥጥር መመሪያ ማእቀፎች የተዘረጉ እንዲሁም መሻሻሎች የታዩ ቢሆንም ፣ የዲጂታል አገልግሎት ተጠቃሚነት እና ዘመናዊ የመተግበሪያ አማራጮች በማምጣት ረገድ ሃገሪቱ አሁንም ገና ጅምር ላይ ነች። ይህንን በተሻለ ሁኔታ ለመቀየር የብሔራዊ ባንክ፣ ቴሌኮም ድርጅቶች፣ ባንኮችን ጨምሮ ሁሉም የግልና የመንግስት መስሪያ ቤቶችና ሴክተር ተዋናዮች ሊተባበሩ ይገባል። ሃገሪቱ በቅርቡ ያዘጋጀችው የብሔራዊ ዲጂታል ክፍያ ስትራቴጂ (2021-2024) በአግባቡ የሚተገበር ከሆነ ለዚህ ቅንጅታዊ አሰራር አስቻይ ሁኔታ የሚፈጥር ይሆናል።