ቴክኖሎጂ እና ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን በድሬዳዋ

የኢትዮጵያ መንግስት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ቅድሚያ ከሰጣቸው አጀንዳዎች አንዱ የሃገሪቱን ዲጂታል ኢኮኖሚ አቅም ማሳደግ ነው። ሃገሪቱ ቀስ በቀስም ቢሆን ዲጂታላይዜሽን የኢኮኖሚ እድገትን በማሳለጥ ረገድ የሚኖረውን ጉልህ አስተዋጽኦ የተረዳች ይመስላል።

መንግስትም የዲጂታላይዜሽን ትልሞችን ተግባራዊ ለማድረግ በ2012 ዓ.ም ‘ዲጂታል ኢትዮጲያ 2025’ በሚል የሰየመውን ፍኖተ-ካርታ ይፋ በማድረግ ወደ ስራ ገብቷል። አስተዳደሩ እንደ መሪ ስትራቴጂክ እቅድ የነደፈው ይህ ፍኖተ ካርታ የክልል መንግስታት በዲጂታላይዜሽን ሂደቱ እንዲወጡ የሚጠበቅባቸውን ሚና ያትታል። ስለዲጂታል ከባቢ ግንዛቤና እውቀትን የማሳደግ እንዲሁም በመንግሥት አገልግሎቶች ውስጥ የዲጂታል አሰራር እንዲዘረጋ ማድረግን ከሚጠበቅባቸው ሚናዎች ውስጥ አካቶ ይጠቅሳል።

ይሁን እንጂ እነዚህን የእቅድ አቅጣጫዎች ወደ ተግባር የመቀየሩ ሂደት ገና ጅምር ላይ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። አሁን ላይ አብዛኛዎቹ የሃገሪቱ የዲጂታላይዜሽን እንቅስቃሴዎች ፣ ከእነዚህም ውስጥ ከዲጂታል ስርዓት ጋር የተገናኙ ኢንቨስትመንቶች ፕሮጀክቶችና ጥናቶች ፣ የኢኮኖሚ ማእከልና ዋና ከተማ በሆነችው አዲስ አበባ ውስጥ የተወሰኑ ናቸው።

ከአዲስ አበባ ውጪ ያሉ የዲጂታል እንቅስቃሴዎችን ለመቃኘት ኬ-ፍሊፕ በቅርቡ ድሬዳዋን ጎብኝቷል።

Digitalization in Dire Dawa

ድሬዳዋ ከሁለቱ በቻርተር ከሚተዳደሩ (ራስ-ገዝ) ከተማ መስተዳድሮች አንዷ ስትሆን ከሃገሪቱ ዋና ከተማ አዲስ አበባ (ሌላኛዋ ራስ-ገዝ ከተማ) 500 ኪ.ሜ በስተምስራቅ በኩል ትገኛለች። ከኢትዮጵያ ትላልቅ ከተሞች ውስጥ የምትጠቀሰው ይህች የስምጥ ሸለቆ ምስራቃዊት ከተማ ግማሽ ሚሊዮን ያህል ነዋሪዎች አሏት።

ለጅቡቲ ካላት ቅርበት እና ከጎረቤት ሃገራት ጋር በሚያስተሳስር ዋና የንግድ ኮሪደር ውስጥ መገኘቷ ድሬዳዋን ወሳኝ የኢኮኖሚ ማእከል አድርጓታል። የዛሬይቱ ድሬዳዋ ከተማ ምስረታ በ19ኛው ክፍለ-ዘመን መባቻ (1886 ዓ.ም) አዲስ አበባን ከጅቡቲ ከሚያገናኘው የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር ሃዲድ ዝርጋታ መጀመር ጋር የተቆራኘ ነው። የድሬዳዋ ሰዎችም (*ነዋሪዎችም) ከተግባቢነት ባህሪያቸውና ቀለል ካለ የአኗኗር ዘይቤያቸው ባሻገር ልክ እንደ ከተማቸው ሁሉ ምንጊዜም አዲስ ቴክኖሎጂን ለመልመድ ከፍተኛ መሻት ያላቸው ስለመሆናቸው ይመሰክርላቸዋል።

በአጠቃላይ የከተማዋ መገኛ፣ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታና መናኸሪያነት ብሎም የነዋሪዎቿ ከዘመን ጋር ተራማጅነት ድሬዳዋን ከአዲስ አበባ ውጭ ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ ለሚደረጉ ሽግግሮችና እድገቶች ተመራጭና አይነተኛ መዳረሻነት እንድትታሰብ ያደርጋሉ። ታዲያ ይህን ለማሳካት በዚህች ከተማ ምን እየተደረገ ነው?

መሰረተ ልማት

የተሟላ መሰረተ-ልማትና ለዛም የሚሆን አስቻይ አቅም መገንባት ለሃገሪቱ የዲጂታል ምህዳር መስፋፋትና ለአጠቃላይ የምጣኔ ሃብት እድገት ወሳኝ መሆኑ እሙን ነው። የቴሌኮም ፣ የኤሌክትሪክና የመንገድ አገልግሎቶች ተደራሽ መሆን እና የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን በቅርበት ማግኘት ዜጎች በዙሪያቸው ካለው ከባቢ ጋር በቀላሉ እንዲገናኙና ሁኔታዎችን እንዲረዱ ያደርጋል። ፈጣን የግንኙነት ምህዳርና ለዛም አማራጮች መኖራቸው ግለሰቦችን ለመረጃ ይበልጥ ቅርብ ያደርጋል ፣ ክህሎቶችን ለመፍጠርና ለማሳደግ እድሎችን ይፈጥራል እንዲሁም ገቢንና የፈጠራ ችሎታን ለማሳደግ በተጨባጭ ይረዳል። የበይነ-መረብ ተጠቃሚነት መጨመር ከሃገራት ምጣኔ-ሃብታዊ እድገት መፋጠንና የጥቅል አመታዊ ገቢ እድገት ጋር አዎንታዊ ትስስር ሊኖረው እንደሚችል ማሳያዎች አሉ።

በኢትዮጵያ የቴሌኮም የኔትዎርክ ሽፋን ባለፉት አመታት ከፍተኛ መሻሻል አሳይቷል። በመንግስት ባለቤትነት የተያዘውና የሃገሪቱ ግዙፍ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ የሆነው “ኢትዮ-ቴሌኮም” የአገልግሎት ሽፋኑ ከሃገሪቱ መልክአ-ምድር 85 በመቶ ያህል መድረሱን ይገልፃል።

ታዲያ ድሬዳዋ እና ነዋሪዎቿም አስተማማኝ የሚባል የቴሌኮም አገልግሎት ያገኛሉ። የቴሌኮም አገልግሎት በከተማዋ ለሚደረጉ የዕለት ተእለት እንቅስቃሴዎች በተለይም ለንግድ እና ማህበራዊ ግንኙነቶች በጣም መሰረታዊ ነው።

በድሬ የበይነ-መረብ አገልግሎትም በስፋት ጥቅም ላይ ውሏል። ኢትዮ ቴሌኮም የቤት ለቤት “ብሮድባንድ ኢንተርኔት” አገልግሎት ላይ የዋጋ ቅናሽ ማድረግ ስትራቴጂ መከተሉ እንደ አዲስ አበባ ሁሉ በድሬደዋም የአገልግሎቱን ፈላጊዎችና ተጠቃሚዎች ቁጥር ከፍ አድርጎታል።

ምንም እንኳን በክልሎችና በከተሞች ተደራሽነት ተተንትኖ የተገለፀ አሃዛዊ መረጃ ባይቀመጥም ኢትዮ ቴሌኮም የመደበኛ ብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎቱ ተጠቃሚዎችን ቁጥር በ765% በማሳደግ ባለፋት አራት አመታት ብቻ የአገልግሎቱ ደንበኞች ግማሽ ሚሊዮን እንደደረሱ ይፋ አድርጓል።

ይኸው መንግስታዊው የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ በግንቦት ወር 2013 ዓ.ም በድሬዳዋ ከተማ የአራተኛው ትውልድ  “4G” ኢንተርኔት አገልግሎት አስጀምሯል። እስከ 2013 (2021) ዓ.ም ባለው መረጃ  የድሬዳዋ ከተማን ጨምሮ ኢትዮ ቴሌኮም በምስራቅ ኢትዮጵያ ዲስትሪክት 1.3 ሚሊዮን ደንበኞች የተለያዩ አገልግሎቶቹን ይጠቀማሉ።

የፌስቡክ (ሜታ) ማስታወቂያ መተግበሪያን መሰረት ተደርጎ በተወሰደ ግምታዊ አሃዝ በድሬዳዋ እስከ 150,000 የሚሆኑ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች እንዳሉ ይታሰባል።

በቅርቡ በኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፍ የመጀመሪያው የግል አገልግሎት ሰጪ ኩባንያ በመሆን ዘርፉን የተቀላለቀው “ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ” ከጥቂት ሳምንታት በፊት የሙከራ አገልግሎቱን ሲጀምር ድሬዳዋን የመጀመሪያዋ ከተማ አድርጎ መርጧታል። የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች በሳፋሪኮም አማራጭ አገልግሎት የማግኘታቸውን በደስታ የተቀበሉት ይመስላል። የሙከራ አገልግሎቱ በይፋ ሲጀምርም በሺዎች የሚቆጠሩ  ነዋሪዎች ከሳፋሪኮም መደብሮች ሲም ካርድ ለመግዛት ሰልፍ ይዘው ውለው ታይተዋል።

ኬ-ፍሊፕ በከተማዋ ተዘዋውሮ እንደቃኘው በርካታ የድሬዳዋ ነዋሪዎች ዘመናዊ የስማርት ስልክ ተጠቃሚዎች ናቸው። የቴሌኮም አገልግሎት ኔትወርኩን ከማስጀመር ባሻገር በተመጣጣኝ ዋጋ የሞባይል ቀፎዎችን አብሮ በማቅረብ ስራውን የጀመረው የሳፋሪኮም መግባት ደግሞ የስማርት ስልክ ተጠቃሚዎችን ቁጥር ይበልጥ ይጨምረዋል ተብሎ ይጠበቃል።

የድሬዳዋ ከተማ የትራንስፖርትና መንገድ ሁኔታም አመቺ የሚባል ነው። የከተማዋ ዋና ዋና መንገዶቿ አስፋልት የሆኑት ድሬዳዋ የእግረኛና የውስጥ ለውስጥ መተላለፊያ መንገዶቿ ደግሞ በኮብልስቶን ንጣፍ የተሸፈኑ ናቸው። እ.ኤ.አ በ2000ዎቹ የኮብልስቶን መንገድ ንጣፍ ዝርጋታ በኢትዮጵያ ያስጀመረችው ድሬ ነበረች። ዛሬ ላይ በሌሎች የሃገሪቱ አካባቢዎች ተስፋፍቶ ይታያል።

የድሬዳዋ መንገዶች በተለምዶ ‘ባጃጅ’ በመባል በሚታወቁት የባለሶስት እግር ተሽከርካሪዎች (አንዳንዶቹ በሃገር ውስጥ የሚገጣጠሙ ናቸው) የተሞሉ ሲሆኑ አነዚህ ባጃጆች በከተማዋ ዋነኛ የህዝብ ትራንስፖርት አማራጮች ናቸው።

የፋይናንስ አገልግሎቶች

በተጨባጭ እንደሚስተዋለው በፋይናንስ አገልግሎቶች ተደራሽነትና በምጣኔ ሃብታዊ ልማት መካከል ያለው ቀጥተኛ ትስስር የሚያጠያይቅ አይሆንም። በዚህ ረገድ ታዲያ ኢትዮጵያ በፋይናንስ አገልግሎቶች አቅርቦት አካታችነት ዝቅተኛ ከሆኑ ሃገሮች ውስጥ የምትመደብ ነች። ሆኖም ከቅርብ አመታት ወዲህ ፣ በዋነኝነትም ከዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶች መጀመርና የባንኮች ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ፣ መሻሻሎች እንዳሉ ይታያል።

በሃገሪቱ አገልግሎት እየሰጡ ካሉ የንግድ ባንኮች ሁሉም ለማለት በሚያስችል መልኩ በድሬዳዋ ከተማም ቅርንጫፎቻቸውን ከፍተዋል። በመንግስት ባለቤትነት የተያዘው የዘርፉ ግዙፍ ተዋናይ  የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን (ኢንባ) ጨምሮ እንደ አዋሽ ፣ አቢሲኒያ ፣ ዳሽን እና ወጋገን የመሳሰሉ በአንፃራዊነት በዘርፉ የቆዩና ልምድ ያላቸው የግል ባንኮች በድሬ አገልግሎት ይሰጣሉ። እንደ እናት እና ደቡብ ግሎባል ያሉ ትናንሾቹ የግል ባንኮችም በከተማዋ ቅርንጫፎች አሏቸው።

እንደ አማራ ባንክ ያሉ አዳዲስ የግል ባንኮች እንዲሁም ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ አገልግሎት የሚሰጡት ዘምዘም እና ሒጅራ ባንኮችም በድሬዳዋ ስራቸውን ጀምረው ደንበኞችን በማገልገል ላይ ናቸው። በቅርቡ ከማይክሮ ፋይናንስ ተቋምነት ወደ ባንክ አገልግሎት ሰጪነት የተሸጋገሩት ሲንቄ እና ሸበሌ  ባንኮችም በድሬ ስራ ላይ ናቸው።

በኢትዮጵያ ብቸኛው የቤት ብድር እና ተያያዥ ፍላጎቶችን መሰረት ያደረጉ የባንክ አገልግሎቶች ሰጪ የሆነው ‘ጎሕ’ የቤቶች ባንክም በድሬዳዋ ስራ ከጀመረ ወደ ስምንት ወራት አስቆጥሯል። ጎሕ ባንክ በድሬዳዋ እስከአሁን ለአንድ ነዋሪ የሞርጌጅ ብድር ሰጥቷል። ጎሕ ከተመሰረተ በመጀመሪያው አመት የስራ ክንውኑ ከሃገርአቀፍ የሞርጌጅና የንግድ ብድር እንቅስቃሴ ስድስት ሚሊዬን ብር ትርፍ አግኝቷል።

በሃገሪቱ የባንክ ኢንዱስትሪ ያሉ አገልግሎት ሰጪ ባንኮች ከከፈቷቸው አጠቃላይ ቅርንጫፎች ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑት ከዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ውጪ ያሉ ናቸው። በተቃራኒው በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ውስጥ ባሉ አገልግሎት ሰጪ ኩባንያዎች ከተከፈቱት 670 ቅርንጫፎች ውስጥ ግማሽ ያህሉ በአዲስ አበባ ተከማችተው የቀሩ ናቸው።

በድሬዳዋ ከተማ በባንኮች የተተከሉ አውቶማቲክ የገንዘብ መክፈያ (ኤ.ቲ.ኤም) ማሽኖችን በቀላሉ ማግኘት ይቻላል። በሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች ውስጥ እንደሚስተዋለው ሁሉ በድሬዳዋም ማይክሮፋይናንስ ተቋማት በብዛት ይገኛሉ። ከነዚህ በዋነኝነት የሚጠቀሰው በ1996 ስራ የጀመረው ድሬ ማይክሮፋይናንስ ሲሆን የከተማ አስተዳደሩ አካታች የፋይናንስ አማራጮች አስፈላጊነትን ታሳቢ አድርጎ ባደረገው ጥናት የተመሰረተ ነው።

በድሬዳዋ ያሉ የቢዝነስ ባለቤቶች እንደሚሉት የማይክሮፋይናንስ ተቋማት ለፋይናንስ ፍላጎቶቻቸው ዋነኛ መፍትሔ ናቸው። የድሬ ማይክሮፋይናንስ ተቋም ዋና አማራጫቸው ሲሆን የሊዝ ፋይናንስን [በተለይም የማሽነሪ] ጨምሮ የተለያዩ የፋይናንስ አገልግሎቶችን ከተቋሙ ያገኛሉ። የድሬ ማይክሮፋይናንስ እስከ መጋቢት 2014 ዓ.ም ባለው መረጃ ከ8000 በላይ ቋሚ የብድር አገልግሎት ደንበኞች ያሉት ሲሆን 287 ሚሊዬን ብር ያልተከፈለ ብድር አቅርቧል። ከተቋሙ የብድር አገልግሎት ግማሽ ያህሉ ለንግድ ዘርፉ የተሰጠ ሲሆን የተቀረው በኮንስትራክሽንና ሌሎች ዘርፎች ላሉ የተመቻቸ ብድር ነው።

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳድርም ለአነስተኛና ጥቃቅን አንቀሳቃሾች (ኢንተርፕራይዞች) የብድር አገልግሎት ያመቻቻል። 1,397 ለሚሆኑና በ1,822 ግለሰቦች የሚንቀሳቀሱ ነባር የአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች በመስተዳድሩ በኩል በድምሩ 283 ሚሊዬን ብር የብድር አገልግሎት ባሳፍለነው ሳምንት ተመቻችቶላቸዋል። በተመሳሳይም 580 ለሚሆኑ አዳዲስ የአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች በድምሩ 94 ሚሊዮን ብር እንዲሁም 33 ኢንተርፕራይዞች ለካፒታል ፋይናንስ የሚሆናቸው 27.2 ሚሊዬን ብር የብድር አገልግሎት አግኝተዋል።

የድሬዳዋ ነዋሪዎች የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎቶች ተጠቃሚ ናቸው። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ  ‘ሲቢኢ ብር’ ፣ ቴሌ-ብር፣ ኢ-ብር፣ እንዲሁም እንደ ሄሎ-ካሽ ያሉ አማራጭ የባንኪንግ መንገዶችን ይጠቀማሉ። የሲቢኢ ሞባይል ባንኪንግ በከተማዋ ከባንክ ወደ ባንክ ለሚደረጉ የገንዘብ ልውውጦች ተመራጭ ሲሆን ኢ-ብር ደግሞ ለተለያዩ ክፍያዎች ጥቅም ላይ ይውላል።

ኬ-ፍሊፕ ያናገራቸው የድሬዳዋ ነዋሪዎች እንደሚሉት የኢትዮ ቴሌኮም ቴሌ-ብር የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት በከተማይቱ ገና ሰፊ ቅቡልነት ያገኘ አይመስልም። በድሬዳዋ እንዲህ ይሁን እንጅ ቴሌብር ይፋ ከተደረገበት ግንቦት 2013 ጀምሮ በሃገር-አቀፍ ደረጃ 25 ሚሊዬን ያህል ተጠቃሚ ደንበኞችን አግኝቷል።

ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ

በግንቦት ወር 2013 ዓ.ም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርና በፌዴራል የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር ትብብር በተዘጋጀ አንድ የስልጠና መድረክ ላይ ንግግር ካደረጉት መካከል የቀድሞው የድሬደዋ ምክትል ከንቲባ አቶ አህመድ መሐመድ ነበሩ። አቶ አሕመድ አፅንኦት ሰጥተው ካነሷቸው ጉዳዮች ውስጥ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራን ከመጠቀምና ከመተግበር በዛም ታግዞ የከተማዋን ችግሮች ለመፍታትና ኢኮኖሚዋን ለማሳደግ ከመሞከር ረገድ ገና እጅግ ብዙ ስራ እንደሚቀረው ነው።

የአቶ አህመድ ንግግር አሁንም እውነትነት አለው። ምንም እንኳን በከተማዋ አስቻይ የመሰረተ-ልማት ፣ የንግድ እንቅስቃሴና ስለ ዲጂታል ከባቢ በቂ ግንዛቤ ቢኖርም የፈጠራ ስራዎችን በማፍለቅና በማጎልበት ረገድ ያለው ጥረት በጣም ዝቅተኛ ነው። የከተማ መስተዳድሩ የሚሰጣቸው የመንግስት አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ የማድረጉ ስራም እንዲሁ ደካማ ነው። 

ሆኖም ግን ጥቂት ተስፋ ሰጪ ጅምሮች እየታዩ ነው። ለምሳሌ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የታክስ ባለስልጣን የክፍያ ሲስተሙን ከቴሌ-ብር የሞባይል የክፍያ አማራጭ ጋር አስተሳስሮ የዲጂታል ክፍያ አሰራርን እየተገበረ ነው።

በአጠቃላይ በዲጂታላይዜሽን ረገድ ያሉ ስራዎች ደካማ ቢሆኑም አንዳንድ በከተማዋ የሚገኙ የግል የቢዝነስ ተቋማት ወደ ዲጂታል ከባቢው በጉልህ በመግባትና አሰራሮቻቸውን በዛ ማእቀፍ በመቃኘት አሻራቸውን ለማሳረፍ ጥረት እያደረጉ ነው። ከነዚህ ውስጥ ተጠቃሽ ሊሆን የሚችለው ‘ባማ የመዝናኛ ማእከል’ ነው።

ከባማ የመዝናኛ ማዕከል ጀርባ ትውልድና እድገቱ በድሬዳዋ ከተማ የሆነው መስራቹ ዳንኤል ታደሰ አለ። ባማ በድሬዳዋ ሰፊ የቢዝነስ ስራዎች ውስጥ ያለ ሲሆን በስሩ የልጆች መጫወቻ (ጌም) ዞን ፣ የአይስክሬም መሸጫና ሬስቶራንቶችን ይዞ ያስተዳድራል። ዳንኤል ስራውን ሲጀምር ከባማ አገልግሎቶችን የማዘዣ ሲስተም በመፍጠር ይህንንም በከተማዋ ‘ሳቢያን’ በሚባለው አካባቢ ባለው የ’ድሬ ሞል’ ውስጥ በከፈተው ሬስቶራንት እንዲሰራበት በማድረግ ነበር። ባማ ይህንን ሲስተም አዲስ አበባ በሚገኙ የሶፍትዌር ባለሙያዎች ያሰራው ስራዎቹን በቀላሉ ለመቆጣጠርና በአግባብና በተጠያቂነት ለማስተዳደር እንዲረዳው በማሰብ ነው። ዳንኤል አብዛኞቹ የባማ ደንበኞች አገልግሎቶቸን ለማግኘት በስልክ ትእዛዝ ሲጠይቁ በማስተዋሉ ትእዛዞችን በኦንላይን ሲስተም የመቀበል የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት እንደሚቻል አምኖ ትዕዛዝ መቀበያና ማድረሻ  ሲስተም ለመዘርጋት እየተዘጋጀ ይገኛል።

እንደባማ ሁሉ በድሬዳዋ ሌሎች የግል ዘርፉ ቢዝነስ አንቀሳቃሾችም የዲጂታይዜሽን አሰራሮችን በመዘርጋት ረገድ ምሳሌ እየሆኑ ነው። ‘ሬጋን ቴክኖሎጂስ’ የተባለው የቴክኖሎጂ ድርጅት በከተማዋ የሶፍትዌር ፈጠራ ስራ ላይ ተሰማርቷል። ድርጅቱ በከተማዋ ለሚገኘው ‘አርት ሆስፒታል’ የኦንላይን አስተዳደር ሲስተም ዘርግቷል። ሬጋን ከዚህ በተጨማሪም ዲጂታል የደመወዝ መክፈያ ስርአትና የጌም ሲሙሌተር ሶፍትዌርን በራሱ በመፍጠር በመኪና መለማመጃ ጌሞች ላይ እንዲጫን አድርጓል።

‘ታክሲ-ቫ’ የተባለው የራይድ አገልግሎት ሰጪ ድርጅት ደግሞ የድሬዳዋ የትራንስፖርት ገፅታ የሆኑትን ባጃጆች አገልገሎታቸውን በዲጂታል ስርአት ለማገዝ በከተማዋ ውስጥ በከፈተው ቢሮው ውስጥ እየሰራ ይገኛል።  ‘ፈረስ’ የተባለውና በአዲስ አበባ እውቅና ካገኙ የታክሲ አገልግሎት ሰጪዎች አንዱ የሆነው ድርጅትም አገልግሎቶቹን በድሬዳዋው ለመጀመር አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

ከአዲስ አበባ አንፃር ሲታይ በድሬዳዋ የትራንስፖርት ዋጋ ውድ ነው። የባጃጅ አገልግሎት ሰጪዎች በቅርቡ ከተደረገው የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያ ጋር አያያዘው ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ አድርገዋል። ለዋጋ መወደዱ አንድ መነሻ የሆነው መንግስት እየተገበረ ያለው የታለመ የነዳጅ ድጎማ ስርአት በከተማው ሙሉ ለሙሉ አለመጀመሩ ነው።  

ይህ እንዳለ ሆኖ ፣ ምንም እንኳን የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የስራ ክህሎትና የቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ የፈጠራ ክህሎትን የሚያበረታቱ ውድድሮች እንዲሁም የምክክርና ስልጠና ፕሮግራሞችን የሚያዘጋጅና የሚሰጥ ቢሆንም፣ በድሬዳዋ ከተማ እስካሁን የፈጠራ ስራን መሰረት ያደረጉ አገር-በቀል ጀማሪ ኩባንያዎችን (start ups) ለመፍጠርና ለማበረታታት የሚያስችልና የሚያበቃ ማእከል አይገኝም።

የክህሎትና እውቀት ሽግግር

በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ስር ያሉ ሁለት የመንግስት የቴክኒክና ሙያ ማዕከላት በቴክኖሎጂ ዙሪያ ያተኮሩ የስልጠና ዓይነቶችን አካተው የከተማዋን ወጣቶች ያሰለጥናሉ።

የድሬዳዋ ዩንቨርሲቲ በከተማዋ የቴክኖሎጂ እውቀትን ከመፍጠርና የቴክኖሎጂ ፈጠራን ታሳቢ ላደረጉ እንቅስቃሴዎች ማእከል ከመሆን ባሻገር ለከተማዋ የዲጂታል ሽግግር ጅምሮች ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል። በስሩ የተለያዩ የትምህርት ፕሮግራሞች ያሉት ዩንቨርሲቲው በ2011 ዓ.ም ከድሬዳዋ የኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማትን ታሳቢ ያደረገ የዲጂታል ግንዛቤና ትምህርት ፕሮግራም ይፋ አድርጎ ማሰልጠን ጀምሯል። በተጨማሪም በዩንቨርሲቲው የቢዝነስ ዴቬሎፕመንት ዳይሬክቶሬት ስር ለመንግስት ሰራተኞች የኮምፒዩተርና ዲጂታል ክህሎት ስልጠናዎችን ይሰጣል።

ከትልቁ የድሬዳዋ ዩንቨርሲቲ በተጨማሪም ሪፍት ቫሊ ዩንቨርሲቲ እና ሉሲ ኮሌጅ የተባሉ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በከተማዋ አሉ። የከተማ መስተዳድሩና የግል ትምህርት ተቋማት ከቴክኖሎጂና ኢንፎርሜሽን ኮምዩኒኬሽን (ICT) ጋር የተገናኙ አጫጭር ኮርሶችን የሚሰጡ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ተያያዥ ስልጠናዎችን ይሰጣሉ።

የስራ እድል ተግዳሮቶች

የከተማ (በተለይም የወጣቶች) ስራ አጥነት የተለያዩ ሃገራት ፖሊሲ አውጪዎችን በእጅጉ እያስጨነቀና እየፈተነ የመጣ ችግር ነው። ኢትዮጵያ ደግሞ በአለም ላይ ከአጠቃላይ ህዝብ ብዛታቸው የወጣት ቁጥር ከፍተኛ ከሆነባቸው ሃገራት አንዷ ናት ። ከሃገሪቱ ህዝብ 70 ከመቶ በላይ የሚሆነው እድሜው ከ29 አመት በታች ነው።

በመሰረቱ ወጣት ማህበረሰብ ለአንድ ሃገር እምቅ ሃይል ሲሆን የወጣቶች ቁጥር መብዛት ለሃገር እድገት የሚያበረክተው ሚና ከፍተኛ ነው። ሆኖም ይህ ሊሆን የሚችለው በሃገሪቱ ከወጣቱ ቁጥር ጋር የተጣጣመ የስራ እድልና የስራ ፈጠራ የሚያበረትታ አስቻይ ሁኔታ ሲኖር ብቻ ነው። ይህ ካልሆነ ግን በተቃራኒው የስራ ኃይል በመባከኑ እንዲሁም የወጣቱ የመግዛት አቅም ስለሚዳከም ለኢኮኖሚ እድገት ሌላ እንቅፋት ይሆናል።

የወጣት ማህበረሰብ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ በሚያድግበት፣ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገው ፍልሰት በየጊዜው በሚጨምርበት፣ በየአመቱ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እየተመረቀ የሚወጣ በሺዎች የሚቆጠር ወጣት ቁጥር ባለበት ሁኔታ በሃገሪቱ ስራ የማግኘቱን ዕድል ጠባብ የማድረጉና የስራ ፈላጊው ሰው ሃይልና የስራ እድሉ ያልተጣጣሙበት ስርአት መፈጠሩ እሙን ነው።

ታዲያ በድሬዳዋ ውስጥም ያለው ሁኔታ በሃገርአቀፍ ደረጃ የሚስተዋለውን ይህንኑ የስራ አጥነት ቀውስ የሚያንፀባርቅ ነው። በ2012 የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ(ያሁኑ የማእከላዊ ስታቲስቲክስ አገልግሎት) ያወጣው የዳሰሳ ጥናት ሪፖርት በሃገሪቱ ካሉ ክልሎች በከተሞች ባለ የስራ አጥነት መለኪያ ራስ-ገዝ የሆነችው የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ሁለተኛዋ ከፍተኛ የከተማ ስራ አጥ ቁጥር ያለባት እንደሆነች ያሳያል ። ትግራይ በ23.3 በመቶ በከተሞች ከፍተኛ የስራ አጥነት ያለባት ክልል ስትሆን የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በ21 በመቶ የአማራ ክልል ደግሞ በ20.4 በመቶ የችግሩ ስፋት ያለባቸው ተከታታይ ክልሎች እንደሆኑ ዳሰሳው ያመለክታል። በከተሞች የሴቶች ስራ አጥነት ከፍተኛ ከሆነባቸው ክልሎች ድሬዳዋ በ32 በመቶ ከፍተኛ ስራ አጥነት የተመዘገበባት ሆናለች።

እንደ ማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲው ግምት በድሬዳዋ 21,000 ያህል ዕድሜያቸው ለስራ የደረሱ ሰዎች ስራ አጥ ናቸው።

አዲስ የተቋቋመው የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የስራ ክህሎትና የቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ከተሰጠው ሃላፊነቶች መካከል የስራ እድል ፈጠራ ዋነኛው ሲሆን ቢሮው በአጠቃላይ ፦ የኢንተርፕራይዞች ልማትና ድጋፍ ፣ የገበያ ልማት ፣ የፋይናንስ አገልግሎቶችን ማመቻቸት ፣ ስራ ፈላጊዎችን መመዝገብ ፣ የኢንደስትሪና ሌሎች የመስሪያ ቦታዎች እንዲመቻቹ የማድረግና የእነዚህን ክንውኖች ኦዲትና ቁጥጥር ስራዎች መምራት ይጠበቅበታል።

በባለፈው የበጀት አመት ቢሮው 13 ሺህ 300 ስራ ፈለጊዎችን የመዘገበ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ከ2000 ያልበለጡ ከተለያዩ የሃገሪቱ ዩንቨርሲቲዎች የተመረቁ ወጣቶች ይገኙበታል። ለከተማዋ የስራ እድል በመፍጠር ረገድ የንግድ ፣ አገልግሎት ፣ የማምረቻ (ማኑፋክቸሪንግ) እና የግብርና ዘርፎች በቅደም ተከተል ዋና ድርሻ የያዙ ኢንዱስትሪዎች ናቸው።

 ኬ-ፍሊፕ በድሬዳዋ ተዘዋውራ መቃኘት እንደቻለችው በከተማዋ መካከለኛና ከፍተኛ የስራ ፈጠራ አቅም ያላቸው የቴክኖሎጂ ድርጅቶች የሉም። ይህም ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዘ ክህሎትና የትምህርት ዝግጅት ያላቸው ስራ ፈላጊ ወጣቶች በዘርፉ የስራ እድል የማግኘታቸውን እድል እንዲሁም በዲጂታል ከባቢ ውስጥ የሚኖሩ ስራ ፈጠራዎችን ጠባብ የሚያደርግ ነው። 

በድሬዳዋ የስራ አጥነት ችግሩ ጎልቶ የሚታይ ቢሆንም በከተማዋ ያሉ ቀጣሪዎች ግን የተማረና የሰለጠነ የሰው ሃይል ለቅጥር ሁኔታዎች ተግዳሮት እንደሆነባቸው ያነሳሉ። አለምአቀፍ የልማት ኤጄንሲዎች ከግልና ከመንግስት ተቋማት ጋር በመቀናጀት ወጣቶችን በማብቃት ላይ ያተኮሩ ፕሮግራሞችን በድሬዳዋም ለመተግበር እየሞከሩ ነው። እነዚህ ፕሮግራሞችም በዋነኝነት የስራ እድሎችን በመፍጠር ፣ የፋይናንስ አማራጮችን ተደራሽነት በማስፋት እና ወጣቶች በምጣኔ ሃብት እድገት ውስጥ ያሏቸውን አብርክቶዎች በማሳደግ ላይ ያተኮሩ ናቸው።

በሃገርአቀፍ ደረጃ ተግባራዊ የተደረጉት ‘ከፍታ’ እና ‘ራዕይ’ ተብለው የተሰየሙ ፕሮጀከቶች በኢትዮጵያ የተለያዩ የክልል ከተሞች ሲጀመር በድሬዳዋም መተግበር ጀምረዋል። ‘ከፍታ’ ወጣቶች የተሻለ የስራ አድል እንዲያገኙ ፣ በፈጠራ ስራዎች ውስጥ እንዲሳተፉና በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ድማፃቸውን ማሰማት የሚችሉበችንና የሲቪል ተሳትፏቸውን የሚያሳድጉበትን አቅም ለመፍጠርና ለማገዝ ያለመ ፕሮጀክት ነው። በተመሳሳይ ‘ራዕይ’ ወጣቶች ወደተሻለና ብቁ ወደሚያደርጋቸው እንዲሁም ህይወታቸውን ማሻሻል ወደሚችሉባቸው የስራ ዘርፎች የሚያደርጉትን ሽግግር የሚያግዝ ፕሮጀክት ነው።

መጪው ጊዜ ለድሬዳዋ ብሩህ ይሆን?

በመላ ኢትዮጵያ ያለው የዲጂታል አገልግሎት እየተስፋፋ እንደመሆኑ ድሬደዋም የዲጂታል ኢኮኖሚው ዋነኛ አንቀሳቃሽ የመሆን ተስፋ አላት። ከምንም በላይ የድሬዳዋ ነዋሪዎች አዳዲስ ነገሮችን ለመቀበል ያላቸው ዝግጁነት ይህን ተስፋ እውን ለማድረግ የሚያስችል ይመስላል።

ሆኖም እንደ ድሬዳዋ ነዋሪዎች ምልከታ ከሆነ በሌሎች ከተሞች የተጀመሩ አሰራሮችን አንዳሉ አምጥቶ በድሬዳዋ መተግበር እንደሚጠበቀው ላይሰራ ይችላል። ከተማዋ የራሷ የሆኑ ልዩ ተግዳሮቶች ያሉባት እንደመሆኗ እነዚህን ተግዳሮቶች የተረዳ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የጉዞ ሂደት ብቻ ድሬዳዋን ረጅም ርቀት ሊያስጉዛትና ተጨባጭ ስኬትን ሊያመጣላት እንደሚችል ያምናሉ።

የድሬደዋን መጪ ጊዜ ግን በተስፋ ለማየት የሚያስችል በቂ ምክንያት አለ።

በቅርቡ ይፋ የተደረገውና ለሃገሪቱ የመጀመሪያ ነው የተባለለት “የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና” በድሬዳዋ መመስረቱ ከነዚህ ተስፋ ሰጪ ምክንያቶች አንዱ ነው። የ”ድሬደዋ ነፃ የንግድ ቀጠና”፤ የድሬዳዋ ኢንዱስትሪ ፓርክና የድሬዳዋ ደረቅ ወደብን ታሳቢ አድርጎና አካቶ የተመሰረተ ሲሆን ታሪፍና ቀረጥን ነፃ ከማድረግ ጀምሮ የንግድ ህጎችን የሚያላላና የተሳለጠ የንግድ ልውውጥን የሚፈጥር ቀጠና ነው። በዚህ የንግድ ቀጠና ውስጥ የንግድ የሎጅስቲክስና የማኑፋክቸሪንግ ስራዎች በጥምረት ይሰራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የፌደራል መንግስት የንግድ ቀጠናውን ለማስጀመር አስፈላጊ የህግ ማእቀፎችን ካጠናቀቀ በኋላ የሚኖሩ እንቅስቃሴዎች ድሬዳዋን ወደ ንግድ ቀጠናነት ማሸጋገር ብቻ ሳይሆን ለብዙ ጅማሮዎች መነሻ እና የአዳዲስ ፖሊዎች መሞከሪያ ያደርጋታል ተብሎ ይታመናል።

የዘርፉ ባለሙያዎች የዚህ የንግድ ቀጠና መመስረት የተለያዩ የስራ እድሎችን ከመፍጠርም ባሻገር በቀጠናው ውስጥና ዙሪያ የዲጂታል ቴክኖሎጂ እድገት እንዲኖር እንደሚያደርግ ይገልፃሉ። የሃገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶችም ወደ ቀጠናው የሚገቡ በመሆኑ ከፍተኛ የስራ እድል እንደሚፈጠር አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችም እንደሚስፋፉ ይታመናሉ።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጠና መርቀው በከፈቱበት ቀን በማህበራዊ ትስስር ገፆቻቸው ላይ ባሰፈሩት መልእክትም ይህንኑ ሃሳብ አፅንኦት ሰጥተው አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው “እየገነባናቸው ያሉት ነፃ የንግድ ቃጣናዎች በፍጥነት እየተለወጠ ወደሚገኘው ዓለም የምንቀላቀልባቸው መንገዶቻችን ናቸው። ዞኖቹ ንግድና ኢንቨስትመንትን ከማቀላጠፍ ባለፈ የቴክኖሎጂ አቅማችንን እንደሚያሳድጉ አልጠራጠርም” ብለዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *