የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ሊኖራቸው የሚገባውን ዝቅተኛ የካፒታል መጠን ከሰባት እጥፍ በላይ እንዲጨምር የሚያዝ መመሪያ ተግባራዊ ካደረገ ወራት ተቆጥረዋል። አዲሱ መመሪያ የወጣው የቀድሞው የ10 ሚሊየን ገደብ ከተቀመጠ ከአንድ አመት በኋላ ነው።
ባንኩ የካፒታል ጭማሪ ለማድረግ መታቀዱ በነባር እንዲሁም በሚመሰረቱ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትን ዘንድ የሚታወቅ ነበር። መመሪያው በአገሪቱ ያሉ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት እያደገ የመጣውን የደንበኞቻቸውን ፍላጎት ለማሟላት አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ ዝቅተኛ የተከፈለ ካፒታላቸውን መጨመር እንደሚያስፈልግ ይገልጻል።
ካፒታሎቻቸው ከ75 ሚሊዮን ብር በታች የሆኑ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትም ካፒታላቸውን ለማሳደግ አምስት ዓመታት ተሰጥቷቸዋል። አክሲዮን በመሸጥ ላይ ያሉ ተቋማት ደግሞ በስድስት ወራት ውስጥ ማለትም እስከ ሐምሌ 2015 የመመስረቻ ማመልከቻቸውን ለብሔራዊ ባንክ ካቀረቡ፣ በነባሩ የ10 ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታል እንዲመሰረቱ ተፈቅዷል። ከተመሠረቱም በኋላ፣ የካፒታል መስፈርቱን ለማሟላት ሰባት ዓመት ይኖራቸዋል።
ብሔራዎ ባንክ በ1980ዎቹ መጨረሻ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትን ለማስተዳደር የቁጥጥር ማዕቀፎችን ማውጣት ሲጀምር ለምስረታ የሚያስፈልገው ካፒታል 200,000 ብር (21,000 ዶላር) እንዲሆን ተወስኖ የነበረ ሲሆን፤ በጊዜው ለባንኮች ምስረታ የሚያስፈልገው ደግሞ 75 ሚሊዮን ብር ነበር።
በ2006 ዓ.ም እንደ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ለመመስረት የሚያስፈልገው የካፒታል መጠን በ10 እጥፍ ጨምሮ ወደ ሁለት ሚሊዮን ብር ከፍ ብሏል። ነባር የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትንም ካፒታላቸውን በአሥር እጥፍ እንዲያሳድጉ አምስት ዓመታት ተሰጥቷቸው ነበር። ነገር ግን በ2007 ዓ.ም የማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ካፒታላቸውን በ 6 አመት ወስጥ ወደ 10 ሚሊየን እንዲያሳድጉ ወስኗል። በሥራ ላይ ለነበሩ 36 ገደማ ለሆኑ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትም የ10 ሚሊዮን ገደብ ላይ ለመድረስ ካፒታላቸውን በየአመቱ ደረጃ በደረጃ ለማሳደግ ይጠበቅባቸው ነበር፡፡
በአዲሱ ደንብ መሰረት የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት በአምስት ዓመታት ውስጥ ካፒታላቸውን እንዴት ለማሳደግ እንዳቀዱ የሚያሳይ ስትራቴጂ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መስፈርቶቹ በወቅታቸው መሟላታቸውን ለማረጋገጥ በየጊዜው ሪፖርቶችን የመቀበል ኃላፊነት ተጥሎበታል።
የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት በፋይናንሱ ዘርፍ ያላቸው ሚና እና የሥራ አፈጻጸም
በአጠቃላይ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የፋይናንስ አገልግሎትን አካታችና ተደራሽ ለማድረግ እንዲሁም ክፍተቶችን ለማሟላት የሚያስችሉ መሳሪያዎች ተደርገው ይታያሉ::
ይህም የሆነበት ምክያት የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት በገጠር አከባቢዎች ስሚሰሩና የፋይናንስ አገልግሎቶችን በተለይም ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ላላቸው ግለሰቦችና አነስተኛ የንግድ ሥራዎች ጥቃቅን ብድር ለማቅረብ የታለሙ በመሆናቸው ነው።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ወደ ሙሉ ባንክ የተሸጋገሩትን አራቱን የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትን (ስንቄ፣ ሸበሌ፣ ሲዳማ እና ፀደይን) ሳይጨምር 45 የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት አሉ። ኦሞ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋምም ወደ ባንክ ለማደግ አምስተኛው የማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ይሆናል።
ብሔራዊ ባንክ በ2014 በጀት ዓመት በማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የሥራ አፈጻጸም ዙሪያ በዝርዝር ለፓርላማ ባቀረበው ሪፖርት መሠረት፣ 40 የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት 19.5 ሚሊዮን የሒሳብ ደብተር ባለቤቶችንና ከአራት ሚሊዮን በላይ፣ በድመሩ 73 ቢሊዮን ብር (14% ዓመታዊ ጭማሪ) ብድር የወሰዱ ተበዳሪዎችን ያገለግላሉ። (ይህ መረጃ ወደ ባንክ የተሸጋገሩ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትን ያካትታል።)
ሪፖርቱም ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱ (ሬይስ ማይክሮ ፋይናንስ እና ወሳሳ1) የሞባይል ባንኪንግ እና የኤጀንት ባንኪንግ አገልግሎት እ በ1,452 ወኪሎች አማካይነት ለ200,000 በላይ ደንበኞችን አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ይገልጻል።
የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማቶቹ በመላ አገሪቱ 2,080 ቅርንጫፎች ያላቸው ሲሆን 56.7 ቢሊዮን የሚሆን የቁጠባ ሂሳብ ደንበኞች አሏቸው። ሰኔ 2014 ዓ.ም በወጣ መረጃ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት አጠቃላይ ካፒታል 15.5 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን በአንድ ዓመት ውስጥ ተቋማቱ በድምር 1.3 ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ አግኝተዋል።
የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትን ካፒታል ማሳደግ ለምን አስፈለገ?
የመመሰርቻ፣ የመንቀሳቀሻ እንዲሁም ሌሎች ወጪዎችን ለመሸፈን
በዓይነትና በመጠን እያደገ የመጣው የማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎት ፍላጎት እና እየጨመረ ያለው የሥራ ማስኬጃ ወጪ ለመሸፈን በቂ ካፒታል መያዝ ይፈልጋል፡፡
በኢንዱስትሪው ሥራ ላይ ከተሠማሩት ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ በአሁን ሰዓት ጠንካራ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋምን ለመመስረት ጠንካራ የካፒታል መሰረትን ይጠይቃል፡፡
የማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ማቋቋሚያ ዋና ዋና ወጪዎች የሚከተሉት ናቸው፡
- የመመስረቻ ወጪዎች
የመመስረቻ ወጪዎች ተቋሙን ከመመሥረት፣ የንግድና የሥራ ፈቃድ ከማውጣት እንዲሁም ጽ/ቤት ከማደራጀት ጋር የተያያዙ ልዩ ልዩ ወጪዎችን ናቸው።
2. የቴክኖሎጂ ወጪዎች
የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የደንበኛ መረጃን ለማስተዳደር፣ ግብይቶችን ለመፈጸምና የሥራ አፈፃፀምን ለመከታተል በቴክኖሎጂ ላይ ጥገኛ እየሆኑ መጥተዋል። ይህም የኮምፒውተር ሃርድዌርና ሶፍትዌርን ጨምሮ ለተለያዩ የቴክኖሎጂ ወጪዎች ይዳርጋቸዋል። ባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሁሉም የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት በ 3 ዓመታት ውስጥ የኮር ባንኪንግ ሲስተም እንዲኖራቸውና ስራቸውን ዲጂታል እንዲያደርጉ የሚያስገድድ መመሪያ አውጥቷል። ይህም በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ተቋማቱ የቴክኖሎጂ ኢንቨስትመት እንዲያደርጉ የሚያስገድድ ነው።
.
3. የሰው ኃይል
ተቋማቱ የሥራ ሂደትን ለመቆጣጠርና ለደንበኞች ጥሩ አገልግሎት ለመስጠት የሰለጠነ የሰው ኃይል ያስፈልጋቸዋል። ወጪዎቹ የደሞዝ፣ የስልጠና እና የሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን ያጠቃልላል።
4. የሥራ ማስኬጃ ወጪዎች
እነዚህም ወጪዎች የኪራይና የኤሌትሪክ ፍጆታን ከመሳሰሉት አገልግሎቶች እንዲሁም ከሌሎች የዕለት ተዕለት ወጪዎች ጋር የሚያያዙ ናቸው፡፡
በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ አንድ የማይክሮ ፋይናንስ ቅርንጫፍ ለማቋቋም ቢያንስ ከሩብ ሚሊዮን ብር ወጪ ይጠይቃል። ጥቂት ቅርንጫፎች ያሉትን ዋና መሥሪያ ቤት ለመምራት እስከ አንድ ሚሊዮን ብር የሚደርስ የወር ወጪ ሊያስፈልግ ይችላል።
ለዕድገት
ከፍተኛ ካፒታል መኖሩ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ብዙ ደንበኞችን እንዲያስተናግዱ የሚያስችል አቅም ይፈጥራል ተብሎ ይታመናል።
የብድር አማራጮችን በማስፋት ለጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችና ለግለሰቦች ከፍተኛ ብድር የመስጠት አቅምን ለመገንባት
ይ
የብሔራዊ ባንክ ህግ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ለአንድ ግለሰብ ተበዳሪ የካፒታላቸውን አንድ በመቶ የሚበልጥ እና ለአንድ ተበዳሪ ቡድን የካፒታላቸውን አራት በመቶ የሚበልጥ ብድር እንዳይሰጡ ይከለክላል። ካፒታላቸውን ማሳደግ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ለደንበኞቻቸው ከፍ ያለ ብድር እንዲሰጡ ያስችላቸዋል። ይህም ለጥቃቅን፣ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የተለየ ጠቀሜታ ይሠጣል፡፡
ተወዳዳሪ ሆነው ለመገኘት
የባንኮች ቁጥር መጨመር እንዲሁም የወጭ ባንኮች ወደ ሀገሪቱ እንዲገቡ መታቀዱን ተከትሎ በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ ከፍተኛ ውድድር የኖራል ተብሎ ይገመታል።
ባንኮች ደንበኞቻቸውን ለማብዛት የሚያደርጉት ጥረት እይተሰፈፋ በሄደ ቁጥር የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትም ነባር ደንበኞቻቸውን ይዞ ለመቆየትና አዲስ ደንበኞችንም ለማፍራት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። ይህ ደግሞ በቂ ካፒታል ይፈልጋል።
ተግዳሮቶች
በሰኔ 2014 ዓ.ም ወደ 18 የሚጠጉ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የ75 ሚሊዮን የካፒታል አሟልተዋል።
የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት አመሰራረት ሁኔታ ካፒታል የሚያሳድጉበትን መንገድና ሁኔታ የሚወስን ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት አወቃቀራቸው ሦስት ዓይነት ናቸው። የመጀመሪያዎቹ በክልል መስተዳደሮች የተቋቋሙና በባለአክሲዮንነት የሚያሰተዳድሯቸው ናቸው። ሁለተኞቹ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የሚደገፉ ሲሆን፤ የተቀሩት ደግሞ በግለሰብ ባለአክሲዮኖች የሚተዳደሩ የንግድ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ናቸው።
መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ግለሰቦች በክልል መስተዳደሮች በሚደገፉ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ባለአክሲዮን ሊሆኑ ይችላሉ።
የአማራ የብድርና ቁጠባ ተቋም፣ የኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ፣ የሲዳማ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም፣ የኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም፣ የሶማሌ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም እና አዲስ የብድርና ቁጠባ ተቋምን ጨምሮ በክልል መስተዳደሮች የሚደገፉ ተቋማት ወደ ባንክ ተቀይረዋል፣ እይተቀየሩም ይገኛሉ። እነዚህ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ጥሩ አፈጻጸም ያላቸውና በአብዛኛው በየክልላቸው ያሉ ማህበረሰቦችን የሚያገለግሉ ናቸው።
ወደ ባንክ የመቀየር ሂደታቸውን በማጠናቀቅ ላይም እያሉ፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የክልል መስተዳደሮች በአንድ ማይክሮፋይናንስ እስከ 70 በመቶ ብቻ የባለቤትነት መብት እንዲኖራቸው አድርጓል።
መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅት የሚደገፉ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት በተወካይ ባለአክሲዮኖች (symbolic shareholders) የሚተዳደሩ ሲሆን፣ አብዛኛውን ጊዜ የሚቋቋሙት በውጭ የልማት ድርጅቶች የሚተገበሩ ፕሮጀክቶችን ለማካሄድ ነው። እንደ እሸት፣ ግዮን እና ጋሻን ያሉ ተቋምት በዚህ መንገድ የተመሰረቱ ናቸው።
መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የሚደገፉ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የትርፍ ድርሻ ስለማይከፍሉ ካፒታላቸው በየአመቱ እያደገ ይሄዳል። በዚህም ምክንያት፣ የካፒታላቸውን ለማሳደግ የተሻለ እድል አላቸው።
ይሁን እንጂ እንበልና 10 ሚሊየን ካፒታል ያላቸው የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት 60 ሚሊዮን ብር ማሰባሰብ ቢኖርባቸው፤ ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት በየዓመቱ 12 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ ወይም ከትርፋቸው እንደገና ኢንቨስት ማድረግ ይኖርባቸዋል።
በአሁኑ ሰዓት ወደ 60 የሚጠጉ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት በመመስረት ላይ ይገኛሉ። በርካቶች ከ10 ሚሊየን ብር በላይ አሰባስበው ወደ ገበያ ለመግባት እየጣሩ ቢሆንም፣ በ6 ወራት ውስጥ የአክሲዮን ሽያጩን ለመጨረስ ፈታኝ ሊሆን ይችላል። የ 6 ወር ገደቡ ካለፈ ግን አንደ ተቋም ለመመስረት የሚጠበቅባቸውን 75 ሚሊዮን ብር ማሟልት የጠበቅባቸዋል፡፡
ማዕከላዊ ባንኩ በ2013 ዓ.ም ለባንኮች የሚያስፈልገውን ካፒታል በአሥር እጥፍ ለማሳደግ ሲወስን ተመሳሳይ አካሄድ ተከትሎ ነበር። በወቅቱ የነበሩ ባንኮች መስፈርቱን ለማሟላት አምስት ዓመታት ሲሰጣቸው አዳዲስ ባንኮች ደግሞ ሰባት ዓመታት ነበሯቸው።
በምስረታ ላይም የነበሩ ባንኮች በቀድሞው 500 ሚሊዮን ብር ካፒታል ለመመስረት የስድስት ወር ጊዜ ተሰጥቷቸው ነበር። ነገር ግን ገንዘቡን ማሰባሰብ ያልቻሉት አብዛኞቹ እንዲፈርሱ፣ የንግድ መስመራቸውን እንዲያሻሽሉ ወይም አምስት ቢሊዮን ብር ለማሰባሰብ አክሲዮን መሸጥ እንዲቀጥሉ ተገደዋል።
መጪው ጊዜ ለማይክሮ ፋይናንስ ዘርፍ ምን ይመስላል?
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በ2012 ዓ.ም የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ወደ ባንክ እንዲሸጋገሩ የሚያስችል መመሪያ አውጥቷል። ይህን ተከትሎ በዋነኛነት በክልል መስተዳደር የሚደገፉ በርካታ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ሽግግራቸውን ጀመሩ።
እነዚህ በመንግስት የሚደገፉ ትላልቅ የማይክሮ ፋይናንስ ድርጅቶች በተሳካ ሁኔታ ወደ ባንክ መቀየራቸው፣ ለነባርና ለአዳዲስ ተቋማት ሰፊ ገበያ ይከፈታል።
በ2014 መጨረሻ ላይ የኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ (ሲንቄ ባንክ)፣ የሶማሌ ማይክሮ ፋይናንስ (ሸበሌ ባንክ)ና የአማራ የብድርና ቁጠባ ተቋም (ፀደይ) ወደባንክነት ሲያድጉ፣ አጠቃላይ የቁጠባ ተቀማጭ ገንዘብ በ44.6 በመቶ የቀነሰ ሲሆን ለደንበኞች የተሰጠ ብድር ደግሞ በ40 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል።
እነዚህ ተቋማት የማይክሮ ፋይናንስ ደንበኞቻቸውን ማገልገል ግዴታችው ቢሆንም የባንክ ስራ ላይ መሰማራታቸ በዘርፉ ክፍተት ሊፈጥር እንደሚችል ይገመታል።
ይህም እያደገ ከመጣው በገጠሩ አካባቢ የፋይናንስ ፍላጎትና በገጠር አካባቢዎች የሚደረጉ በርካታ የገንዘብ ድጋፍ ስራዎች ጋር ተዳምሮ ባንክ ያልደረሰባቸውን ቦታዎች ለመድረስ ለተቋማቱ ሰፊ ገበያ ይፈጥራል።
አብዛኛዎቹ መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅት የሚደገፉ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ሌሎች ቀጥተኛ የገንዘብ ድጋፎችን ጨምሮ የፋይናንስ አገልግሎት ተደራሽነትና የገንዘብ ልገሳ ሥራዎችን ለማመቻቸት የተመሰረቱ ናቸው።
ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት አንጻር የኢትዮጵያ ማይክሮ ፋይናንስ ዘርፍ ገና በማደግ ላይ ይገኛል። 213 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ናይጄሪያ ከ800 በላይ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋምት ሲኖሯት ታንዛኒያ ከ500 በላይ አላት ።
የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት በዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶች የመሳተፍ እንዲሁም ደንበኞቻቸውን ተጠቃሚ የማድረግ ትልቅ እድል አላቸው።
በሬይስ ማይክሮ ፋይናንስ የቀረበውና በምስራቅ ኢትዮጵያ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው የሰሀይ ሞባይል ዋሌት ለዚህ ማሳያ ነው።
_________________________________
1 ሪፖርቱ የትኞቹ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የሞባይል ዋሌትና የወኪል መረብ እንዳላቸው አይገልጽም። በኬ-ፍሊፕ ግምገማ፣ ሬይስ ማይክሮ ፋይናንስ ሰሀይ የተባለ የሞባይል ዋሌት አለው። ወሳሳ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋም የራሱ የወኪል መረብ አለው።